ጊዜ የማይሽረው ታላቅነት በኢትዮጵያ የእግር ኳስ መድረክ

Uncategorized

በዮናስ ድንቁ

ለአመታት የኢትዮጵያውያን ኩራትና ድምቀት ሆኖ የቆየ፣ ብዙዎች ለስኬቱ ምስክር የሚሆኑለት፣ የስመጥር ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ማረፊያ፣ ዘመኑ ወደኋላ ሲቆጠር በትላንትና ዛሬ መሀከል በውጤቱ የሚኮሩ ብዙ ደጋፊዎችን መፍጠር የቻለ ባለብዙ ታሪክ ባለብዙ ድል ፈር ቀዳጅ አርበኛ ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ።
እኛም በዛሬው ‘ከስፖርት ማህደር’ አምዳችን ስለዚህ ታሪካዊ ክለብ ብዙ ብዙ ልንላችሁ ወደድን። መልካም ንባብንም ተመኘን።

እስኪ ወደኋላ እንሂድ፣ 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ አራዳ ሰፈር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ – ክርስትያን አካባቢ – ጆርጅ ዱካስ የሚባል ወጣት ቤት ውስጥ። አየለ አትናሽ እና ጆርጅ ዱካስ የእግርኳስ ክለብ ለመመስረት ሲያስቡ አየለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ተማሪ ስለነበር በዛን ጊዜ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ለነበሩት ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ሀሳባቸውን ነገሯቸው። አዎንታንም ስላገኙ ለቡድኑ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ፍለጋ ተጀመረ። ብዙዎች ግን ፈቃደኛ አልነበሩም። ጊዜው ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር እያኮበኮበ የነበረበት ወቅት ስለነበር ለዛንጊዜ ወጣቶች እግር ኳስ የሚለው ነገር ወደ ጭንቅላታቸው የሚመጣ የመጨረሻ ሃሳብ ነበር። ይሄን የተጫዋቾች እጥረት ለመፍታትም ይድነቃቸው ተሰማን አስፋልት ሲሻገር አጊኝተውት እንዲቀላቀላቸው አግባብተው ይወስዱታል።
በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያው ጨዋታም በዛን ጊዜ ከነበረው የ አርመን አራራት ክለብ ጋር ተደረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስም ይድነቃቸው ራሱ ባስቆጠራቸው ጎሎች የአርመኑን ክለብ 2-0 በመርታት የአሸናፊነት ጉዞውን ሀ ብሎ ጀመረ።

እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ከ 1929 እስከ 1934 ዓ.ም ኢትዮጵያ በጣልያን ቁጥጥር ስር በነበረችበት ጊዜ ይህ ክለብ የሃገራዊ አንድነትና የህዝቡ የነፃነት ምሳሌ ለመሆን ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም። ይህ ግን ጣልያኖችን ያስከፋ ነገር ሆነ። ድሮውንም ቢሆን ጣልያን ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ለመውረር ሲመጣ ሽንፈትን ቀምሶ የተመለሰበት ቀኑ የዋለው የጊዮርጊስ እለት ስለነበር ጊዮርጊስ የሚለውን ስም አይወደውም ነበር።
በቀጥታ ክለቡን ለማፍረስ ብዙ ሙከራ ቢያደርጉም ያልተሳካላቸው ጣልያኖች ግን የራሳቸውን ‘6ኪሎ(Cenco Maje)’ የተባለ ክለብ በመመስረት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማዳከም ትግል ገቡ።የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከ ጣልያኑ ክለብ ጋር የሚያደርጓቸውን ብዙዎቹን ጨዋታዎች ቢያሸንፉም በጨዋታዎቹ መጨረሻ ላይ ግን በአራዳ ፖሊስ (በዛን ጊዜ በጣልያን የሚመራ) የሚደርስባቸው ድብደባ ቀላል የሚባል አልነበረም። ይህ ግን ተጫዋቾቹን ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ ተነሳሽነታቸውን ይበልጥ ጨመረው። በዚህ የትንቅንቅ ወቅትም ክለቡ ስሙን ወደ ሊቶሪዮ ዉቤ ሰፈር እንዲቀይር ተገዶ ነበር።

ፋሺስት ኢትዮጵያን ለቆ ከወጣ በኋላም ቢሆን በ 1938 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሲጀመር ተሳትፎ ካደረጉት 5 ክለቦች ውስጥ ኢትዮጵያን በመወከል ብቸኛ ክለብ ነበር። የሃገሪቱ አብዮት ተቀስቅሶ የደርግ ስርአት የሃገር ውስጥ የእግር ኳስ ክለቦችን እንደ አዲስ ሲያዋቅር ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ ቢራ በሚል ስም መጠራት ጀመረ። በዚህ ስምም ለ20 አመታት በሊጉ ውስጥ ቆይቶ በ 1980ዎቹ በአዲስ አደረጃጀት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በሚል አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ጉዞውን ቀጠለ።
ክለቡ የራሱ የሆነ እግር ኳስ ሜዳ ግንባታ ለመጀመር ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን ለዚህም መሳካት የክለቡ የበላይ ጠባቂ የሆኑት የሳውዲው ቢሊየነር ሼህ መሃመድ ሁሴን አል አሙዲ 80% የሚሆነውን ወጪ ይሸፍናሉ። የተቀረውን 20% ደጋፊው የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ከራሱ አውጥቶ እንዲሸፍን ይደረጋል።

በ 2010 ዓም ክለቡ በቢሾፍቱ ከተማ መርቆ ያስከፈተው መጠሪያውንም በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ የሰየመው አካዳሚም በአሁን ሰዓት ለክለቡ ብሎም ለሃገሪቱ እግር ኳስ የወደፊት ተስፋ የሚሆኑ ታዳጊ ተጫዋቾችን በማፍራት ላይ ይገኛል። ይህ አካዳሚ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የፈሰሰበት ሲሆን በአንድ ጊዜ እስከ 100 የሚጠጉ ታዳጊዎችን ማስተናገድ ይችላል። በውስጡም 2 የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ የመመገቢያና የመልበሻ ክፍሎች፣ ጂም፣ ዘመናዊ የህክምና ሴንተር እና የመኖሪያ ዶርሚተሪዎችን አካቶ የያዘ ነው።

ክለቡ ከ 1992 ዓም ጀምሮ ባለቤትነቱ ከፋይ ወደሆኑ ደጋፊዎች የተሸጋገረ ሲሆን በቅርቡ ብዙውን አክሲዮኑንም ለደጋፊዎቹ እንደሚሸጥ አስታውቋል። አሁን ላይ እንመለስና ባሳለፍነው የካቲት ወር አጋማሽ ላይ በተደረገው 83ኛ የክለቡ አመታዊ ስብሰባ ላይ የበላይ አመራሮቹ እና ደጋፊዎቹ በተገኙበት የአክስዮን ሽያጭ የሚጀምርበትን ቀን ጨምሮ የተለያዩ ዝርዝር ጉዳዮችንም ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ እንደዚህ ክለብ በውጤት ያሸበረቀ ክለብ የለም። 27 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ (ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ 14) ዋንጫዎች፣ 12 የኢትዮጵያ ካፕ ዋንጫዎች፣ 16 የኢትዮጵያ ሱፐር ካፕ ዋንጫዎች፣ 5 የአዲስ አበባ ከተማ ካፕ ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለ ሲሆን ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ካፕ ኦፍ ሻምፒዮን ክለብስ ለ10 ጊዜያት መሳተፉ ከኢትዮጵያ ብቸኛ ክለብ ያደርገዋል።

ቡድኑ ባለበት ቦታ ሁሉ የማይቀሩት ደጋፊዎቹ አዲስ አበባም ላይ ይጫወት ሌላ ቦታ በቢጫና ቀይ ቀለሞች አጊጠው በህብረ ዝማሬ ተውበው አካባቢውን ጥልቅ ድምቀት ያለብሱታል። ነገር ግን በሁሉም ጭንቅላት ውስጥ የሚመላለስ አንድ ጥያቄ አለ……..
ክለቡ በሀገር ውስጥ ያለው ብልጫና ስኬት በአህጉር ደረጃ የሚደገመው መች ይሆን? ይህ የሁላችንም ጥያቄ ይመስለኛል። አበቃሁ።

#ተጨማሪ

ዋና አሰልጣኝ ፡ ስቴዋርት ሃል
ረዳት አሰልጣኝ ፡ ዘሪሁ ሸንገታ
ቅፅል ስሞች ፡ ፈረሰኞቹ
ሳንጃው
አርበኛው
አራዶቹ
ፕሬዝደንት ፡ አቶ አብነት ገብረመስቀል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *