ዋናው መተንፈስ ነው

March – አረንጓዴ

ቤተልሄም አምባቸው


ከተማችን አዲስ አበባ ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ ከመጣው የነዋሪዎቿ ቁጥር ጋር ተያይዞ ትክክለኛ የሆነ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ጉዳይ ዋነኛ የከተማዋ ጥያቄ መሆን ከጀመረ ሰንቷል፡፡ በመኖርያ መንደሮች ፣ በጋራ መኖርያ ህንፃዎች ፣ የንግድ ቦታ በሚበዛባቸው አከባቢዎች ወዘተ እዚህም እዛም የተከመሩ ቆሻሻዎችን ማየት የእለት ተእለት አጋጣሚ ነው፡፡ የዚህን ችግር ስፋት በመገንዘብ ኢንቫይሮመንት ፈርስት ቻሪተብል ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የካቲት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ከመስቀል አደባባይ ተነስቶ መገናኛ ድረስ የደረሰ የከተማ ፅዳት ፕሮግራም “Walk and Pick Trash To Cash” በሚል መሪ ቃል አዘጋጅተው ነበር፡፡ ኢንቫይሮመንት ፈርስት ቻሪተብል ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ በሀገራችን እና ከሀገራችን ውጪ ያሉ በጎ ፈቃደኞችን በማሰባሰብ በከባቢ ጥበቃ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የግንዛቤ ስራዎችን በማከናወን በቀጣይነት መንግስት እደረገ ያለውን ሀገር አቀፋዊ አረንጓዴ ልማት መደገፍ
መልካምነትን ፣ በጎነትን ፣ ቀናነትን ፣ ትህትናን ፣ አገልጋይነትን ፣ ለኛነትን ፣ ተፈጥሮአዊነትን እና አለም ዓቀፍ የመልካም ልቦች ስብስብን ለማበረታታት ብሎም መርሆቹን በህብረተሰቡ ዘንድ ለማስረፅ በማሰብ የተቋቋመ ማህበር ነው፡፡ የፕሮራሙ አላማም የነበረው የከተማ ፅዳት ጉዳይ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሀላፊነት መሆኑን ማስገንዘብ እና ቆሻሻ ተብለው ከሚጣሉ ነገሮች ላይ ገቢ ማግኘት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለተሳታፊዎች ማሳወቅ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይም የከተማ ፅዳት
ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡ በማለዳ ከመስቀል አደባባይ የተነሳው የፅዳት ዘመቻ መጨረሻውን መገናኛ ቫምዳስ ሲኒማ አድርጓል፡፡ በሲኒማ ቤቱ በነበረው ፕሮግራም ላይም የተለያዩ ባለሙያዎች የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ በዚህም የከተማ ፅዳት ከተማን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የሚኖረው ጥቅም ትኩረት ተሰጥቶበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ንፁህ ያልሆነ ከተማ የሚኖረውን የጤና እና ተያያዥ ችግሮች ሲጠቀሱ ተደምጠዋል፡፡ ከተማን ፅዱ ማድረግ የእያንዳንዱ ነዋሪ ግዴታ ነው፡ ፡ በዚህም መሰረት የሚከተሉትን መንገዶች ብንከተል ጽዱ ፣ ለኑሮ ምቹ ፣ ያልተበከለ እና ጤናማ ከተማን መመስረት እንችላለን፡፡ ከተማችንን ፅዱ ለማድረግ ልንከተላቸው የምንችላቸው ቀላል መንገዶች እነዚህን ቀላል እና ውጥታማ መንገዶች ብንከተል ብዙ ድካም እና ወጪ ሳይኖረው ከተማችንን ፅዱ ማድረግ እንችላለን፡፡

  1. እቃዎችን በፌስታል የምንገዛ ከሆነ የራሳችንን ፈስታሎች ይዘን ለመሄድ እንሞክር ድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ የወረቀት ቦርሳዎችን የሚያቀርቡ ሱቆች ወይን ሱፐር ማርኬቶች ሀገራችን ላይ በብዛት የሉም፡፡ ስለዚህም የራሳችንን የእቃ መያዣ ፌስታሎች ወይንም ሌሎች የቦርሳ አይነቶቸን እቃ ለመሸመት ስንሄድ ይዘን ብንሄድ የሚጣሉትን የፌስታል መጠኖች ስለምንቀንስ ከተማችን ፅዱ እንዲሆን እናደርጋለን፡፡
  2. የቤት ውስጥ ቆሻሻዎችን በሶስት መጣያዎች እንለያቸው በተፈጥሮ የሚበሰብሱ ፣ እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ እንዲሁም ሌሎች በማለት የቤት ውስጥ ቆሻሻዎችን በሶስት በመክፈል ለማስወገድ እንሞክር፡፡ በዚህም ተግባር በከተማችን የሚከማቹ ቆሻሻዎችን እንቀንሳለን፡፡ ከዚህም ባሻገር የከተማ ፅዳት ባለሙያዎችን በስራቸው እናግዛቸዋለን፡፡
  3. የፕላስቲክ ውሀ መያዣዎችን ደግመን የምንጠቀምባቸውን መንገዶች እንፈልግ በአካባቢያችን የፕላስቲክ ኮዳዎችን ለድጋሚ ጥቅም የሚያውሉ ድርጅቶች ካሉ እቃዎቹን ለነሱ በመሸጥ ገንዘብ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በኮዳዎቹ ሊሰሩ የሚችሉ ሌሎች ነገሮችን ለመስራት እንሞክር፡፡ ለምሳሌ የአበባ መትከያዎችን ፣ የቤት ውስጥ ጌጦችን ወዘተ ለመስራት ልንጠቀምባቸው እንችላለን፡፡
  4. የኮምፖስት ጉድጓድ ለመፍጠር እንሞክር በቀላሉ ሊበሰብሱ የሚችሉ የምግብ ትራፊዎችን እንዲሁም የአትክልት እና ፍራፍሬ ልጣጮችን ዝም ብለን ከመጣል እና የበሽታ መራብያ ከማድረግ ይልቅ በኮምፖስት መልክ አዘጋጅተን ለተለያዩ አትክልቶች ማዳበርያነት መጠቀሙ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ ምናልባትም ይህንን ለማድረግ የምንኖርበት አካባቢ ምቹ ካልሆነ ኮምፖስተን በመስራት ላይ ለተሰማሩ ሰዎች ልጣጮቹን እና የምግብ ትራፊዎቹን መስጠት እንችላለን፡፡
  5. የአካባቢ ፅዳት ቡድኖችን እንመስርት ካሉም እንቀላቀላቸው የአካባቢ የፅዳት ስራን ለብቻችን ከምንከውነው ይልቅ በቡድን ሆነን ብንሰራው የበለጠ ውጤት ማግኘት እንችላለን፡፡ ስለዚህም ባካባቢያችን
    የሚገኙ ነዋሪዎቸ ጋር በመሆን የፅዳት ቡድኖችን በመመስረት የፅዳት ስራን ለመከወን እንሞክር፡፡
  6. የጨርቅ የእቃ መያዣ ቦርሳዎችን እንጠቀም ከጨርቅ የተሰሩ የእቃ መያዣ ቦርሳዎችን መጠቀም የከተማን ፅዳት ለመጠበቅ የምንወስደው ሌላው አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በቀላሉ የማይበሰብሱ እና ከባቢን የሚበክሉ ፈስታሎች በየቀኑ ከመጠቀም ይልቅ ደጋግመን ልንጠቀመው የምንችለው እና ከባቢን የማይበክለውን ከጨርቅ የተሰራ የእቃ መያዣን መጠቀሙ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡
  7. በመንገድ ዳር የተቀመጡ የቆሻሻ መጣያዎችን በአግባቡ ይጠቀሙ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በየመንገድ ዳሩ የተቀመጡ የቆሻሻ መጣያዎች አሉ፡፡ እነዚህን የቆሻሻ መጣያዎች በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ ፅዱ ከተማን መፍጠር ይችላሉ፡፡
  8. የቤትዎን ፅዳት የመጠበቅ ልምድዎን ያዳብሩ ቤት ውስጥ ያሎት ልምድ ከቤት ውጪ ለሚኖሮት እንቅስቃሴ ማረቂያ ነው፡፡ ቤቶን በንፅህና የመጠበቅ ልምድ ካሎት ያንኑ ልምድ ወደ አካባቢዎት በቀላሉ ይዘውት ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ይህንን ልምድ በቤቶ በማዳበር ለልጆችዎን እና በአካባቢዎ ላሉ ሌሎች ሰዎች አርአያ መሆን ይችላሉ፡፡