ናዝራዊትን ታደጉልን – ቤተሰቦችዋ

News

ወጣት ናዝራዊት በተጠረጠረችበት የአደንዛዥ ዕፅ ማዘዋወር ወንጀል ተይዛ በቻይና ፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለች ሶስት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በነዚህ ወራትም ቤተሰቦችዋ ናዝራዊትን ነፃ ለማውጣት ያደረጉት ጥረት ምንም ውጤትን እንዳላስገኘላቸው ነው ከወጣቷ እህት ቤተልሄም አበራ ጋር በስልክ ባደረግነው ቃለ መጠይቅ መረዳት የቻልነው፡፡ ወጣቷ አብሮ አደግ ጓደኛዋን አምና የተቀበለችው “ሻምፖ” ውስጡ ሌላ ነገር የመሆኑን ዜና ከሰማች በኃላ በከፍተኛ መረበሽ ውስጥ ቆይታለች፡፡ ከቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሊያናግሯት የሄዱት ሰዎችም ይህንን ነበር ማረጋገጥ የቻሉት፡፡

ምንም እንኳን ሶስት ወራትን በእስር ላይ ብታሳልፍም እስከ አሁን ድረስ ግን ፍርድ ቤት አልቀረበችም ብላናለች እህቷ ቤተልሄም አበራ፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ቆንፅላ ፅ/ቤቱ በቀጠረላት ተከላካይ ጠበቃ አማካኝነት ክርክሯን ለማድረግ የመረጃ መሰብሰብ ሂደቶችን እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የ”ሻምፖው” ባለቤት እጣ ፋንታስ?
ለናዝራዊት ይህንን አደንዛዥ ዕፅ ሰጥታለች የተባለችው አብሮ አደግ ጓደኛ ምንም እንኳን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለች ቢሆንም አሁን ግን በ20 ሺህ ብር ዋስ ተለቃለች፡፡ “ያለንን ማስረጃ እንኳን ፖሊሶቹ ሊሰሙን ፈቃደኞች አልሆኑም ስትል ነበር ቤተልሄም በምሬት ለመልካም74 ሁኔታውን ያስረዳችው፡፡ “አሁንም” ትላለች ቤተልሄም “አሁንም ቢሆን ያሉንን ማስጃዎች በሙሉ ለሚመለከተው አካል ለመስጠት ፈቃደኞች ነን፡፡ የእህታችንን ነገር ብቻ እልባት እንዲያገኝ የሚመለከተው አካል እገዛ ያድርግልን፡፡”

በአሁኑ ሰዓት በማህበራዊ ድረ-ገፆች እየተነገረ ያለው መረጃ አብዛኛው ከእውነት የራቀ ስለሆነ ሰዎች መረጃውን ከማጋራት እንዲቆጠቡ የተናገረችው ደግሞ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች የናዝራዊት ጓደኛ ናት፡፡ በዚህም መሰረት ከቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመጣ ጥያቄ መሰረት ማንኛውም አይነት የኦን ላይን አቤቱታዎችን ከመፈረም ህዝቡ እንዲቆጠብ ቤተሰቦችዋ መልዕክታቸውን እያስተላለፉ ለእህታቸው በማሰብ ለተደረገው ነገር እና ህዝቡም ላሳየው ትብብር ከልብ አመስግነዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *